Ethiopians


Amharic Poems  ግጥሞች

በዚህ ገጽ በተለያዩ ታዋቂ ገጣሚያን የተጻፉ የአማርኛ ግጥሞች ያገኛሉ

 መሸ ደግሞ አምባ ልውጣ!

አምባ ወጥቼ እኩለ-ሌት ፤ ስለት ገብቼ በስሟ
ከርሞ ሰይጣን በሷ አስቶኝ፤ ልገላገል ከህመሟ
ጠበሏ አፋፍ በጨረቃ፤ ደጋግሜ፤ ማህሌት ቆሜ
ሆዴ ቃትቶ ባር ባር ብሎ፤እርቃኔን ከሷ ታድሜ
ደጀ ሰላሟን በአራት እግር፤ ተንበርክኬ ተሳልሜ
በስጋዬ እሚነደውን፤ በጸሎት ላቤ አጣጥሜ
እፎይ ብዬ አመስግኜ፤ ውዳሴዋን ደጋግሜ...
ገና ከደጅዋ እልፍ ሳልል፤ ደሞ ይምጣ የቁም ህልሜ?
ሌት በጥምቀቷ የነጣው፤ ነጋ፤ ደፈረሰ ደሜ።
ለሷ እንጂ ለኔ አልያዘልኝ፤ አዬ የስለት አታምጣ!
በውጣ ውረድ በጠበል፤ ባሣር ወዜ ቢገረጣ
ልክፍቷ እንደሁ አልለቀቀኝ፤ መሸ ደሞ አምባ ልውጣ!

ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድሀን፣ እሳት ወይ አበባ!
 መሆን አለመሆን

በመሆን እና ባለመሆን
በማድረግ እና ባለማድረግ
በሁለት ታዛዦች ስር መውደቅ ነው
ሰው የመሆን ትልቅ ህግ
ሊኖሩት በማይፈቅዱት ህግ
ሊፈጽሙት በማይሹት ስህተት
በጣምራ ግጭቶች መሃል መቆም ነው ሰው የመሆን ሰውነት
ይሄ ሁሉ ፍጡር ይሄ ሁሉ ፍጡር
በፍጥረት መድረክ ላይ የሚርመሰመሰው
ላንዲት ቅጽበት እንካን ሰው ሆኖ አያውቅም ሰው ሊሆን ጽንስ ነው
ሰው እስኪሆን ድረስ አንዳንድዜ አምላክ አንዳንዴ ሰይጣን ነው።

ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን

 መሄዴ ነው

ባር ባር አለው ሆዴ ልቤ መሬት ለቆ
ሊያከንፈኝ እንዳይሆን አለግብሩ መጥቆ
አለአስተዳደጉ አለባህሉ ወድቆ
ሽው እልም ሽው እልም ልቤ ወፌ ይላላ
በመስተፋቅር ቀስት በሮሮ ምህላ
እንደደመና አክናፍ እንደጮራው ጥላ
ሽው እልም ሽው እልም ሽው እልም ይላላ
ነሸጠው ሸፈጠ ሄደ ሸመጠጠ
በመስተፋቅር ቀስት በሮሮ አመለጠ።


ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን

ክልክል ነው

ማጨስ ክልክል ነው
ማፍዋጨት ክልክል ነው
መሽናት ክልክል ነው
ግድግዳው በሙሉ ተሰርቶ በክልክል
የቱ ነው ትክክል?
ትንሽ ግድግዳና ትንሽ ኃይል ባደለኝ
"መከልከል ክልክል ነው"፤ የሚል ትዕዛዝ አለኝ፡፡


(በእውቀቱ ስዩም፣ የ፣ሣት ዳር ሐሳቦች፣ 2000)

 
 
 «በጠራ ጨረቃ»

በጠራ ጨረቃ በእኩለ ሌሊት
አይኖቿ እያበሩ እንደ ከዋክብት
«ሳማት ! ሳማት !» አሉት
«እቀፍ ! እቀፋት።»
አላወላወለም ወጣቱ ታዘዘ
ወገቧን አንገቷን እጇን በእጁ ያዘ
ምንም እንኳ ጡቷ እንደሾህ ቢዋጋ
ጣቷ በመሆኑ የጉማሬ አለንጋ
ጆሮ ግንዱን ሰማው በጥፊ ሲናጋ።
ዋ ጀማሪ መሆን ! ዋ ተማሪነት
ዋ ትእዛዝ መፈጸም ዋ ምክር መስማት !
በጠራ ጨረቃ በኩለ ሌሊት...

መንግስቱ ለማ
 ወሰደው ከፊትዋ

ልጅነት ሆነና ዕረፍት የሌለበት
አንገት ያለሃሳብ የሚመዘዝበት
ልብ ከግንባር ላይ የሚነበብበት
ለጋነት ባጠራው ይሉኝታ ቢስ ፊትዋ
በስልት ያልተገራው ግልጽ አስተያየትዋ
መልሶ ቢያሳየው የራሱን አንካሳ
የባህሉን ጅራፍ የወጉን ጠባሳ
“ምነው ዓይን በላች ይሉኝታ አጣችሳ”“
እያለ ጮኸና ልቧን አስበርግጐ
ወሰደው ከፊትዋ ልጅነትዋን ጠርጐ
በሞረድ ምላሱ ፈግፍጐ ፈግፍጐ . . .

(ታገል ሠይፉ፣ ቀፎውን አትንኩት፣ 1986)

 ጠላቴን ስመርቅ

በስልጣን ከፍ ከፍ
በዝና ከፍ ከፍ
በሀብትም ከፍ ከፍ
ወደላይ ከፍ ከፍ
ከፍ ከፍ.... ከፍ ከፍ
ከዛ የወደቅህ ዕለት አጥንትህ እንዳይተርፍ::

ገጣሚ ታገል ሰይፉ

 

 

 

 ደመወዙን ቢጥል
አንስተው ጠጡበት
ባርኔጣውን ቢጥል
ወስደው ደመቁበት
ከዘራውን ቢጥል
ተመረኮዙበት
በሄደበት ሁሉ
እየተከተሉ
በጣለው ሲያጌጡ
በጣለው ሲያተርፉ
ራሱን ሲጥል ግን
አይተውት አለፉ

በውቀቱ ስዩም
(ካንድምታ ላይ የተወሰደ )
 

 ፍቅር ጥላ ሲጥል

በገና
ቢቃኙ፡
ሸክላ
ቢያዘፍኑ
ክራር
ቢጫወቱ፡
ለሚወዱት
ምነው
ሙዚቃ
ቢመቱ
ቢቀኙ
ቢያዜሙ
ቃል
ቢደረድሩ
ጌጥ
ውበት
ቢፈጥሩ
ቤት
ንብረት
ቢሠሩ
አበባ
ቢልኩ
ደብዳቤ
ቢልኩ
ምነው ______
ቢናፍቁ !
አገር
ቢያቋርጡ ______
ቢሔዱ
ቢርቁ
ዓመት
ቢጠብቁ
ዘመን
ቢጠብቁ።
ለሚወዱት ምነው ....

ገብረ ክርስቶስ ደስታ

1998፡ 96-97

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ያንድ አፈር አፈሮች

ፍቅራችንን ድንበር ወሰን ላይገድበው
ሁለት ክልል ላይመጥነው
መገዳደል ፍት ላይሆነው
በሽንፈትህ እሰይ ላልል
በሽንፈቴ እፎይ ላትል
ከቂም በቀል ፍቅር ላይበቅል
ልጅህ በጄ ለምን ይሙት
ልጄስ በጅህ ለምን ትሙት
እኔና አንተ እኮ
ያንድ እናት ልጆች
ወንድማማቾቸ
ያንድ አፈር አፈሮች
ርስት አፈሩማ ይቅርም ወደዚ ይሂድም ወደዛ
ያው ነው የኢትዮጵያ ያንድ አፈር መጠሪያ
ወዲያ ካለው የቀድሞዋ ወዲህ ካለው የስካሁና
ግዳይ ጥዬ በልጅህ ደም በጀግንነት ላልጠራ
ግዳይ ጥለህ በልጄ ደም ላትፎክር ላታቅራራ
ወንድም ገለው ላይፎክሩ ጀብዱ ሰርተው ላይኩራሩ
ያዘን ሙሾ ሊዘምሩ
እንደማተብ የእምነት ክር ፍቅር ድሩ ላይበጠስ
በሃዘናችን ላትዘፍኑ በሞታችሁ ላንደንስ
ስውር አይሁን ነጭ ሴራው ደስ አይበለው የጠላት ነፍስ
ልጅህ አይሙት በልጄ ጣት ልጄም አይሙት በልጅህ ቀስት
እኔና አንተ እኮ ከዘመናት በፊት
በታሪክ በሃይማኖት በባህል በትውፊት
በደስታ በችግር ስም የለሽ ስመ ጥር
በጋሻና በጦር ጀብደኛ ባላገር
የአንድ አያቶች ዘር የሁለት አፈር ሰፈር
ስም የለሹን ጥጋብ ስመጥር በረሃብ
እያሉ ሲተቹህ እያሉ ሲተቹን በሙጫ ስድብ አጣብቀውን
ሲተቹን መተቸት ሲተቹህ መተቸት እንዳለ ስናውቀው እንዳለ ስታውቁት
ካንድ እናት ተወልደህ በሁለት አባት አድገን
ባንድ ውሃ ተራጭተን አንድ አፈር አቡክተን
ቃታ ስንሳሳብ እሺ ላይለው ልብህ ደስ ላይለው ልቤ
እኮ እኔና አንት ዛሬ እንዲህ እንጫከን
እኔና አንተ እኮ
ያንድ እናት ልጆች
ወንድማማቾቸ
ያንድ አፈር አፈሮች

እናም ወንድም ስማኝ ልስማህ ደስ አይበለው ነገር ሰሪ አንተን ከኔ ፀብ ሲያቃባ
እንዘምር ባንድ እንዝለል ወሰን አይኑር የደም ካባ
በመሞትህ ደስ ላይለኝ ውስጥ ልቤ እዥ ሊያነባ
የናቱ ልጅ ልጅን ገድሎ ላያሰማ ጉሮ ወሸባ
ፍቅር እንጂ ግድባችን ወሰን አይኑር የደም ካባ…………

ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 ሃገሬ

አገሬ ውበት ነው
ለምለምና ነፋስ የሚጫወትበት
ጸሃይ የሞላበት፣ ቀለም የሞላበት።
አገሬ ቆላ ነው፣ ደጋ ወይና ደጋ
እዚያ ብርሃን አለ ሌሊቱ ሲነጋ።
አገሬ ተራራ ሸለቆ ረባዳ
አገሬ ጅረት ነው ገደልና ሜዳ።
ውሸት ነው በበጋ ጸሃይ አትፋጅም
ክረምቱም አይበርድም፣
አይበርድም፣ አይበርድም።
አገሬ ጫካ ነው
እንሰሳት አራዊት የሚፈነጩበት
በወጥመድ ሳይገቡ ሳይነካቸው ጠላት።
እዚያ አለ ነጻነት።
በሃገር መመካት፣
በተወላጅነት፣
በባለቤትነት፣
እዚያ አለ ነጻነት።
አገሬ ሃብት ነው።
ጎመኑ ስብ ጮማ፣ ቆሎ ክትፎ ስጋ
ድርቆሹ ፍትፍት ነው፣ ቃሪያው ሙክት ሠንጋ።
ጠጁ ነው ወለላ
ከኮኛክ ይነጥቃል የመንደሩ ጠላ።
እህሉ ጣዕም አለው እንጀራው ያጠግባል
በዓሉ ይደምቃል፣
ሙዚቃው ያረካል፣
ጭፈራው ዘፈኑ ችግርን ያስረሳል።
እዚያ ዘመድ አለ።
ሁሉም የናት ልጅ ነው፣
ሁሉም ያባት ልጅ ነው፣
ጠላትም አንዳንዴ ይመጣል መቃብር
ባለጋራም ቸር ነው “ያገር ልጅ ሲቸገር” ።
ገነት ነው አገሬ።
ምነው ምን ሲደረግ !
ምነው ! ለምን ! እንዴት !
ዘራፊ ቀማኛ ምቀኛ ወንበዴ
ጥርኝ አፈር በጁ ስንዝር ወሰን አልፎ
የተቀደሰውን ያፍሪቃ ላይ ደሴት
ባያገኝ ለማርከስ ጠላት ይመኝ እንዴት።
እምቢኝ አሻፈረኝ !
አሻፈረኝ እምቢ !
መቅደስ ነው አገሬ፣
አድባር ነው አገሬ።
እናትና አባት ድኸው ያደጉበት
ካያት ከቅደመ አያት የተረካከቡት
አፈር የፈጩበት፣
ጥርስ የነቀሉበት።
አገሬ ዓርማ ነው የነጻነት ዋንጫ
በቀይ የተጌጠ ባረንጓዴ ብጫ።
እሾህ ነው አገሬ፣
በጀግናው ልጅ አጥንት የተከሰከሰ
ጠላት ያሳፈረ አጥቂን የመለሰ።
አገሬ ታቦት ነው መቅደስ የሃይማኖት
ዘመን የፈተነው በጠበል በጸሎት።
ለምለም ነው አገሬ፣
ውበት ነው አገሬ፣
ገነት ነው አገሬ።
ብሞት እሄዳለሁ ከመሬት ብገባ
እዚያ ነው አፈሩ የማማ ያባባ።
ስሳብ እሔዳለሁ ቢሰበርም እግሬ
አለብኝ ቀጠሮ ከትውልድ አገሬ።
አለብኝ ቀጠሮ
ከትውልድ አገሬ ካሳደገኝ ጓሮ።

ገብረክርስቶስ ደስታ።
  

 እውነት ለፈለገ....

ፀሀይ ስትገባ
ጥያቄ ይወጣል ፀሀይን ተክቶ
ልቤም እስከንጋት ያልፈዋል ተኝቶ
ግድ ነው በለሊት አዳፍኖ ማለፉ
እሳትን ባመድ ሆድ ጥያቄን በን'ቅልፉ
ከጎረምሶች ከንፈር ጪስ እየነጠቀ
ከኮረዶች ጡት ላይ ሽቶ እየሰረቀ
ነፋሱ ይዞራል
ግና በምላሹ ምስጢር መች ይነግራል
መስኮቴን ብከፍተው
በብርድ ልብሴ ላይ ኮከቦች ፈሰሱ
እውነትለፈለገ ውበት ነው ወይ መልሱ


(በእውቀቱ ስዩም)

 

 

 

 

 

 ድምጽ አልባ ፊደላት

ፀጉሩን አንጨብሮ ፂሙን አጎፍሮ
ጥግ ተቀምጦ ለሚታየኝ ወጣት
ሂድና ታዘዘው ስጠው አንድ ድራፍት
ቅዳለት ደብል ጂን ሃሳቡን ይርሳበት
በፂሙ መጎፈር በፀጉሩ መንጨብረር
ቁጥር ፈታ በሚል በግንባሩ መስመር
ይታየኛል ቃንቃ ይታየኛል ነገር
እዛም ከጨለማው ብቸኝነት ውጣት
ሲጋራዋን ይዛ ለቆመችው ወጣት
ሂድና ታዘዛት የሚጠጣ ስጣት
ምጋ በተፋችው በጭሶቹ መሃል
ሴትነት ሲበደል እህትነት ሲጣል
እናትነት ሲጎድል
ይታየኛል ቃንቃ ይታየኛል ፊደል።


ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን

 

 

 

 

 መቃብሬ ላይ 'ሚጣፍ

ጥብቅ ማሳሰቢያ ሸክላን ለምትሰሩ
እዚህ መቃብር ላይ አፈር አትዝገኑ
ሲነድ ሲቃጠል ሲጨስ በመኖሩ
ሲቃጠል ለሚኖር ....................
ለጀበና መስሪያ አይሆንም አፈሩ ::

ኑረዲን ዒሣ

 

 መሞዘቅ

የምሽት ጨረቃ
ባር ባር በሚል ጣቱኣ
ገርፋ ስትሞዝቀኝ
እኔም የማላውቀው
እሱም የቀኝ
የሆነ ሩቅ ሀገር
አለ ሚናፍቀኝ ::

ኑረዲንኢሣ

 

 

 

 

ስለወሬ ቁመት

ስለ ማቱሣላ እድሜ
መርዘም መንዘላዘል
ሲያስረዳኝ ወንድሜ
ዘጠኝ መቶ አመታት ...
(ያለፈ መሰለኝ )
ሳዳምጠው ቆሜ

 ኑረዲን ዒሣ

 

ሐዘን


ሐዘን የጎበኘው
ደጋግሞ ደጋግሞ ....
መደሰት አይችልም :
ማዘንም አይችልም :
ከመከራ ጋራ ...........
እጅግ ወዝ ተጣግቦ ::

ኑረዲን ዒሣ
(ለሀገሬ ሕዝብ )

 

 

 

 

 

 እኔ ጉልት ስውል ጉልት ይውላሉ
እኔ አሣ ሳሰግር አሣ ያሰግራሉ
እኔ ፍራሽ ሳድስ ፍራሽ ያድሳሉ
ብቻ አመድ ብሸጥም አመድ ይሸጣሉ
ይሄ ሁሉ ሆኖም
ምቅኞች አይደሉም
ሀበሾች ምቅኞች ብላችሁ አትበሉ
እኔ ዛፍ ስተክል መቼ ዛፍ ተከሉ 


ኑረዲን ኢሣ

 

 

 

 

 

 

 

 

 
ከጎራው ዘልቄ እስኪ ልነጋገር
ካለሰው ቢወዱት ምን ያደርጋል አገር?
የኔ ውብ ከተማ
ሕንፃ መች ሆነና የድንጋይ ክምር
የኔ ውብ ከተማ

መንገድ መች ሆነና የድንጋይ አጥር
የኔ ውብ ከተማ የኔ ውብ አገር
የሰው ልጅ ልብ ነው
የሌለው ዳርቻ የሌለው ድንበር፡፡
ሕንፃው ምን ቢረዝም ምን ቢፀዳ ቤቱ
መንገዱ ቢሰፋ ቢንጣለል አስፋልቱ
ሰው ሰው ካልሸተተ ምንድነው ውበቱ?
የሰውን ልብ ነው፡፡
ምን ቢነድ ከተማው ተንቦግቡጎ ቢጦፍ
ቢሞላ መንገዱ በሺ ብርሃን ኩሬ
በሺ ብርሃን ጎርፍ
ምን ያደርጋል?
ምን ያሳያል?
ካለሰው ልብ ብርሃን
ያ ዘላለማዊ ነበልባል ያ ተስፋ ሻማ
ጨለማ ነው
ሁሉም ጨለማ፡፡


ኦሮማይ፣ በዓሉ ግርማ፣ 1984

 

  
    
    
    

Welcome

Recent Photos

 

Featured Products

No featured products

Create a free website at Webs.com